የክፍለ ከተማው የፍትህ ጽ/ቤት ስልጣንና ተግባር

  1. የኤጀንሲዉን ህግ እና ለስራ የሚያግዙ አሰራሮችን መፈጸም እና ማስፈጸም፣ በተገቢዉ አደራጅቶ መያዝ እንዲሁም በወረዳ በአግባቡ መፈፀማቸዉን መከታተል፣
  2. በሕግ ጉዳዮች የክፍለ ከተማውን አስተዳደር ዋና አማካሪና ተወካይ ሆኖ ይሠራል፤
  3. የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ይተገብራል፤ አስፈፃሚ አካላት በዋና ዕቅዳቸው ማካተታቸውን ያረጋግጣል፤ ይደግፋል፤ አፈፃፀሙን ይከታተላል፤ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ያቀርባል፤
  4. ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ፕሮግራም ይቀርፃል፤ ዕቅድ ይነድፋል፤ በሚመለከተው አካል ሲጸድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፤ ይመራል፤ ያስተባብራል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፤
  5. የከተማው አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የአስተዳደሩና የነዋሪው መብትና ጥቅም ወኪል ሆኖ ይከራከራል፣ ያስከብራል፣ የሚከበሩበትን ሂደት ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤
  6. የከተማው አስተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያደርጉትን ውል ይመረምራል፤ ሕጋዊነታቸውን ያረጋግጣል፤ አፈጻጸማቸውን ይከታተላል፤ ተገቢው የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል* ወይም ይወስዳል፤
  7. የከተማው አስተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤትንና የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በመወከል ወይም የከተማ አስተዳደሩንና የነዋሪውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በስሙ በማንኛውም የዳኝነት ሥልጣን በተሰጠው አካል ወይም በግልግል ጉባኤ በመቅረብ ክስ ይመሰርታል፣ መልስ ይሰጣል፣ የጣልቃ ገብ፣ የመቃወም እና የይግባኝ አቤቱታ ያቀርባል፤
  8. የከተማ አስተዳደሩንና የነዋሪውን መብትና ጥቅም ለማስከበር አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በማንኛውም የዳኝነት ሥልጣን በተሰጠው አካል ወይም በግልግል ጉባኤ በመቅረብ በስሙ ክስ ይመሠረታል፤ መልስ ይሰጣል፤ የጣልቃ ገብ አቤቱታ ያቀርባል፤ ይግባኝ ይጠይቃል፤
  9. የተሰጠው ውሣኔ የህዝብንና የመንግስትን ጥቅም የሚጐዳ ሆኖ ካገኘው የመቃወም አቤቱታ ያቀርባል፤ ይከራከራል፤
  10. የአስተዳደሩ ተቋማት ከአሰሪና ሰራተኛ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የክርክር ጉዳዮችን ወክሎ ይከራከራል፤ ያስወስናል፤ ያስፈጽማል፤
  11. በከተማው አስተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤቶች እርስ በእርሳቸው ያልተግባቡባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጪ ባለ አማራጭ የክርክር መፍቻ መንገድ እንዲወሰን ውሣኔ ይሰጣል፤ በውሣኔ መሠረት መፈፀሙን ይከታተላል፤
  12. በሌሎች ሕጐች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በፍርድ ቤት የተያዙ ወይም ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት የማያዋጡ ወይም ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳርጉ ጉዳዮችን በአማራጭ ክርክር መፍቻ ዘዴዎች እንዲፈቱ ያደርጋል፤
  13. በከተማው አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር የዳኝነት ሥልጣን ስር በሚወድቁ የፍትሐብሔር ክስ ለመመሥረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ነዋሪዎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን ፣ አረጋውያንን እና የመሳሰሉትን ወክሎ ክስ ያቀርባል፤ ይከራከራል፤
  14. የገንዘብ አቅም የሌላቸው በከተማው ፍርድ ቤቶች በወንጀል የዳኝነት ሥልጣን ስር በሚወድቁ የወንጀል ተጎጂ የሆኑ ተበዳዮች እንዲካሱ፣ መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከጉዳቱ ጋር የተያያዙ የፍትሐ ብሔር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ያቀርባል ወይም ይደራደራል፤
  15. የሕግ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፤ የከተማው አስተዳደር ያወጣቸው ሕጎች በአግባቡ ስራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ ይጠብቃል፤ የሕግ ወይም የውል ረቂቅ ያዘጋጃል፤
  16. በካቢኔ የጸደቀ ደንብ በአዲስ ነጋሪ ጋዜጣ ያሳትማል፤ የከተማው ሕጎችን መሰብሰብ ማደራጀት መተንተንና ማሰራጨት የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ይፈጽማል፤
  17. ነዋሪው በሕገ መንግስቱና በቻርተሩ የተሰጡትን መብቶችና ነጻነቶች እንዲያውቅና እንዲጠቀም ተገቢውን የሕግ ስልጠና ይሰጣል፤ ለከተማው አስተዳደር አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ለነዋሪው የንቃተ ሕግ ግንዛቤ ይሰጣል፤
  18. በቻርተሩ በተሰጠው ስልጣን መሠረት በከተማው አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቅ ወንጀል የፈጸመ ሰው በሚመለከት ወንጀል ምርመራ በከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ተጣርቶ ሲቀርብለት ወይም እንዲቀርብለት በማድረግ በህግ መሠረት ቀርቦ ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኙ ክስ ያቀርባል፣ ይከራከራል፤
  19. የተጀመረ ምርመራ በህግ መሠረት እንዲቆም ያዛል፣ ክስ ያነሳል ወይም የወንጀል ምርመራ በህግ መሠረት ይዘጋል፣ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፤
  20. በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በውክልና የሚሰጡትን የወንጀል ጉዳዮች ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፤
  21. በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የወንጀል ጉዳዮችን በከተማው ፖሊስ ተጣርቶ ሲቀርብለት ወይም እንዲቀርብለት በማድረግ ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፤ የተጀመረ ምርመራ በሕግ መሠረት እንዲቆም ያዛል፤ ክስ ያነሣል ወይም የምርመራ መዝገቡ በሕጉ መሠረት ይዘጋል፤ ሌሎች ሕጋዊ ተግባራትን ያከናውናል፤ በከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የሚጣሉ የደንብ መተላላፍ ቅጣቶችን ያስፈፅማል፤ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፤
  22. የክፍለ ከተማው አስተዳደር የሚሰጣቸው አስተዳደራዊ ውሣኔዎች ከሕግ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲወሰድ ያደርጋል፤ ምክር ይሰጣል፤
  23. በዐቃብያን ሕግ የሚሰጡ ውሣኔዎች በሕግ መሠረት መከናወናቸውን ያረጋግጣል፤ ጉድለቶችን በጥናት አስደግፎ ይለያል፤ በግኝቱ መሠረትም እንዲታረሙ ያደርጋል፤ አስፈላጊ ሲሆን እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል፤